የጠቅላዩ የኤሜል ምርጫ ፡- የብዙዎች ማላገጫ
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከሰሞኑ እሳቸው ምርጫ ያሉትን ብዙዎች ደግሞ ማላገጫ ያደርጉትን መላ ይሁን ዘዴ ይዘው መጥተዋል፡፡ የምራቸውን ይሁን እቀለዱ በአጋጣሚ ሁን አቅደውበት ባታወቅም በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ለትግራይ ህዝብ ፕሬዝዳንት እጩ በአሜል ላኩ ብለዋል፡፡ ነገርየው በአገሪቱም በአለምም አዲስ የመሆኑን ያህል ብዙዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡
ብዙዎች እዚህ ላይ ማላገጥ ቢቀናቸውም ከቀልዱ መሀል ምንአልባት ቁም ነገር ይኖረው ይሆን ብለው ተስፋ አድርገው ከኢሜል ምርጫው ላይ ትንታኔ ለማውጣት የሞከሩ የዋሆች ነበሩ ፡፡ በዚህም አንዳንዶች ጠቅላይ ሚሩ ጉዳዩ አሳስቧቸው ነው፣ የትግራይ ህዝብ ያለመሪ መቆየቱ ያለ መንግስት ማስተዳደር የሚፈጥረው ችግር አለ ብለው አስበው ነው፣ ችግሩን በኢንተርኔት በታገዘ ቴክኖሎጂ ለመፍታት እየሞከሩ ነው የሚል አሳብ ሲሰጡ ሌሎች ደግሞ እየቀለዱ ነው ብለው ያለፉም አሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የጠቅላይ ሚሩን የልጃልጅ ስነ-ልቦናም እያጠኑ ፖለቲካቸውንም እየተቃወሙ ፣ ወይም የምርም እየደገፉ የተሰጡ አሳቦችን ከየዋሆቹም ከብልሆችም መንደር አሳባስበን እንጨዋወታለን፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት የኢሜሉ ምርጫ የትግራይ ጉዳይ ከእጅ እያፈተለከ በመምጣቱ አጣብቂኝ የፈጠረው የሽንፈት መገለጫ ነው፡፡ አብይ አህመድ ህወሓት ውስጥ ሰርሰርው በመግባት ተላላኪ ለመፍጠር ሞከረው ነበር፡፡ የህወሓት ጉዳይ ራስ ምታት የሆነባቸው ጠቅላይ ሚሩ የፕሪቶሪያ ስምምነት የፈጠረላቸውን ሰላም የተጠቀሙበት ህወሓትን በመከፋፈል እርስ በእርስ ማናቆር ነበር፡፡ ለዚህም ጥቂት ከውስጥ ባንዳ ማግኘታቸው አልረም፡፡ እነዚህም ባንዳዎች የጥገኛ ባህሪ ይዘው በአቶ ጌታቸው በኩል ስራ እየሰሩ ሳለ በሂደት እየተዳከሙ መጥተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ ተሰደዱ፡፡ ይሄ ደግሞ ለአብይ አህመድ ትልቅ ሽንፈት ሆኖ በመገኘቱ አሁንም አለሁ፣ የትግራይ ጉዳይ በቁጥጥሬ ስር ነው የሚለውን ለማሳየት የኢሜል ምርጫውን አመጡ ይላሉ አሳባቸውን የሰጡ ሰዎች፡፡ በኢሜል ምረጡ ማለታቸው አሁንም የትግራይ መንግስት ላይ መሪ የመመደብ እና ምስለኔ የመሾም አቅም አለኝ የሚለውን ለደጋፊዎቻቸው ለማሳየት ነው ይላሉ እነዚህ አሳብ ሰጪዎች::
ቀልድ ነው፡፡ ቀልዱም ቁም-ነገሩም የተደበላለቀበት የኢሜሉ ምርጫ ጠቅላይ ሚሩ እስከአሁን ካመለጧቸው ቀልዶች መካከል አንዱ ነው የሚሉም አልታጡም፡፡ ምንም እንኳን ባያስቅም፡፡ እሰከአሁን የተቀለዱት ቀልዶች ያስቁ ነበር ይኸኛው ግን ያስቃል ሳይሆን ያስንቃል ያሳቅቃል ቢባል ይቀላል፡፡ ከዚህ በፊት ዱቄት ሆነዋል፣ ተበታትነዋል ፣ ከአሁን በኋላ መምራት አይችሉም እየተባሉ የተቀለዱ ቀልዶች ነበሩ፡፡ ያኔም ቀልዶቹ መሬት ላይ እንደማይሆኑ ይታወቅ ነበር ፡፡ የአሁንም በኢሜል መሪ ልምረጥላችሁ የሚለው ባያስቅም አንድ ቀልድ ልንገራችሁ እንደማለት ነው በሚል የወሰዱት ብዙ ናቸው፡፡
የኢሜል ምርጫው ለጠቅላይ ሚሩ የመዝናኛ አማራጭ ነውም ያሉ አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚሩ በስራ ሲወጣጠሩ (ለነገሩ ባይወጣጠሩም) መዝናናት ይወዳሉ፡፡ ከዚህ በፊት እንደ ህፃን ልጅ ሳይቀር ሲዝናኑ አይተናቸዋል፡፡ እንጦጦ ፓርክ ሄደው የመኪና አሻንጉሊት ሲነዱ ፣ ብስክሌት ሲያሸከረክሩ ፣ በመኪና ውሃ ሲረጩ ብዙ ጊዜ አይተናቸዋል፡፡ ምንአልባት የኢሜል ምርጫውም የዚህ መዘናኛ ተቀጥላ ሊሆን ይችላል በሚል ብዙዎች አሹፈውባቸዋል፡፡
የኢሜሉ ምርጫ የንቀት መገለጫ ነው የሚሉ አሳብ ሰጪዎች መነሻው አንጽ 39 ላይ ለማላገጥ ነው የሚመስለው ይላሉ፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት ይህ በትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ህዝብም ላይ የተሰነዘረ የንቀት መገለጫ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ትግልም የራስን እድል በራስ የመወሰን ትግል ነው፡፡ ይሄ ድግሞ መሪዎቼን ራሴ ልምረጥ የሚል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የመብት ጥያቄም የፖለቲካ ፍላጎትም ነው፡፡ ስለዚህ የኢሜሉ ምርጫ የስልጣን ምንጭ ህዝብ ነው የሚለው የፖለቲካ መርህ ላይ የተሰነዘረ ንቀት አድርገው ወስደውታል፡፡
የጠቅላይ ሚሩ የኤሜል ምርጫ እስከአሁን ያስተናገደው ትችትም ሹፈትም ብዙ ነው፡፡ እንኳን የህዝብ መሪ ፣ ፕሬዝዳንት ይቅርና በእድርና በእቁብ ደረጃ ባሉ ትናንሽ ተቋማት የቦርድ ሊቀመንበር ሳይቀር በኢሜል ተመርጦ አያውቅም የሚሉ ወገኖች የቴክንክም የፖለቲካ ጥያቄም አንስተዋል፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑን በመጥቀስ በAI ብቻ አንድን ሰው ሚሊየን ጊዜ እጩ ማድረግ እንደሚቻል በመጠቆም ይሄ ደግሞ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት መብት የሚጥስ ብቻ ሳይሆን የእቃ-እቃ ጨዋታ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ቀልዱ ቢበዛ እንጂ ምርጫውን የምር አያደርገውም ብለዋል፡፡ በመላው አለም ያለ ሰው ሁሉ በኢሜል ለትግራይ ህዝብ መሪ ሊመርጥ ነው ወይ ብለው የጠቀየቁ ሰዎች እንዲህ ከሆነማ የባንግላዴሽም ህዝብም ለትግራይ ህዝብ መንግስት መምረጥ ይችላል ማለት ነው ብለው ጉዳዩ ቁም -ነገር ሳይሆን ቀልድ ስለሆነ ስቃችሁ እለፉት ብለዋል፡፡

Comments
Post a Comment